ክፍል 1: ጥቁር አሜሪካዊው ፓይለት ኮ/ል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን የኢትዮጵያ ቡናማው ጆፌ (The Brown Condor of Ethiopia) “ትውልድና ዕድገት”

➛ የራይት ወንድማማቾች ከምድር ተነስተው በዓየር መብረር በጀመሩበትና ዓለምን ‘አጀብ’ ባሰኙበት 1903 ዓ.ም አንድ ጥቁር ህጻን በፍሎሪዳ ተወለደ። ዘመኑ በአሜሪካ የነጮች የበላይነት የነገሰበት፣ ጥቁሮች እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩበት ስለነበር ይህ ጥቁር ህጻን ለጥቁሮች መኖሪያ በተለየው በገልፍ ፖርት ሚሲሲፒ (gulf port Mississippi) ለማደግ ተገደደ። በሰባት ዓመት እድሜው ለመጀመሪያ ግዜ አውሮፕላን በሰማይ ላይ ሲበር የተመለከተው ህጻኑ ጆን ሲያድግ አውሮፕላን ማብረር እንደሚፈልግ ለእናቱ ይነግራት ነበር። የህጻን ልብ ሆኖ እንጂ በጊዜው አንድ ጥቁር ህጻን እንኳንስ ለአውሮፕላን አብራሪነት እራሱን የሚያጭበት የሰውነት ክብሩም የሚጠበቅበት አልነበረም አገሩ። እናቱም ይህን ምኞቱን ባነሳባት ቁጥር ‘ይህ የነጮች እንጂ የጥቁሮች ስራ አይደለም። ይልቅ ለጥቁሮች የሚፈቀደውን ነገር ለመስራት ብታልም ይበጅሀል።’ እያለች ትመክረዋለች። የጆን ልብ ግን አንዴ ስለሸፈተ ለእናቱ ምክርና ተግሳጽ የሚመለስ አልነበረም። አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር ጆን ገና የ12 ዓመት ልጅ ነበር። ስለጦርነቱ ከሚነገሩ ዜናዎች ለጆን የበለጠ መንፈሱን የሚያነቃው በጦርነቱ ላይ የአሜሪካ የውጊያ አውሮፕላኖች የሚፈጽሙት ጀብዱ ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥቁሮች ት/ት ቤት ሲጀምር በትርፍ ግዜው ጫማ እየጠረገ እራሱንም ቤተሰቡንም መርዳት ጀመረ። ለመካኒካል ነገር ጥልቅ ፍቅር የነበረው ጆን ጫማ በማይጠርግበት ሰዓት ወደ አንድ መካኒክ ባለሱቅ ዘንድ እየሄደ ስራ በመርዳት በ14 ዓመት እድሜው ሹፍርናን ተማረ። ይህም ለጆን አዲስ የስራ እድልን የከፈተ አጋጣሚ ነበር። በሹፌርነት ሞያ እያገለገለ ትምህርቱን ተያያዘው። በዛ ጥቁሮች ለጉልበት ስራ እንጂ ለቀለም እውቀት አይመጥኑም ተብሎ በሚታመንበት ዘመን ጆን በትጋቱና በቤተሰቦቹ እርዳታ ወደ ኮሌጅ የሚያስገባውን ነጥብ በማግኘቱ ለላቀ ትምህርት ከቤተሰቦቹ ርቆ ወደ ተስከጂ ኢንስትቲዩት ተጓዘ። የኮሌጅ ጓደኞቹ ሲናገሩ ጆን ተስከጂ ሳለ ዘናጭ፣ ከሰው ተግባቢ፣ጥሩ ስፖርተኛና ሴት ከመውደዱ ውጪ ምንም ዓይነት ሱስ የሌለበት ወጣት ነበር። ክረምቱን ት/ት ቤት ሲዘጋ ስራ እየሰራ እና ቤተሰቦቹን ጭምር እየረዳ በሞተር ሞያ የኮሌጅ ትምህርቱን አጠናቆ ስራ ፍለጋ ወደ ዴትሮይት (Detroit ) አቀና። ➛ ህይወት በዴትሮይት ዴትሮይት በዘመኑ እያደገ ለነበረው የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ አንዷ ማዕከል ነበረች። ወደ ዴትሮይት ስራ ፍለጋ ነጮቹም ጥቁሮቹም ከየአቅጣጫው ይጎርፋሉ።

ይቀጥላል

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ደራሲያን የፌስቡክ ገጽ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s