ክፍል 3: ጥቁር አሜሪካዊው ፓይለት ኮ/ል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን የኢትዮጵያ ቡናማው ጆፌ (The Brown Condor of Ethiopia) “እንዴት ይህን ለማድረግ ቻልክ?”

….እግቢው ሲገባ ከአንድና ሁለት ትናንሽ አውሮፕላኖች በስተቀር ምንም ሰው አልነበረም። ከዛም ደስ ወደምትባል ባለሁለት ክንፍ ቀይ አውሮፕላን ተጠግቶ በመስታወቱ መስኮት ውስጥ በውስጡ ያሉትን መሪና ማርሽ የመሳሰሉትን ሲያይ እርሱ ይጠግናቸው ከነበሩት ማካኒካዊ ነገሮች የተለየ ምንም ነገር አልነበረውም። በዚህም በመደነቅ ላይ እያለ በድንገት አንድ ሰው “ሄይ አንተ ልጅ ለምንድነው አውሮፕላኑን የምትዞረው?” ሲል በንቀትና በንዴት መልክ ተናገረው፣ ጆንም ደንግጦ ሲዞር አንድ ጸጉረ ቀይ አጭር ወፍራም በመኪና ዘይት እጁና ጸጉሩ የተጨማለቀ ሰው አየ። ከኋላው ግን ንጹህ ሙሉ ልብስ ከነክራባቱ እና የተወለወለ የፈረስ ጋላቢዎች ቦት ጫማ ያደረገ ወጣት ሰው ተከትሎታል። “እዚህ የመጣሁት በአውሮፕላን ለመሄድ ነበር። ስገባ እግቢው ውስጥ ምንም ሰው ስላላገኘው ነው አውሮፕላኖቹን እየተዟዟርኩ ማየት የጀመርኩት። ምንም የነካሁት ነገር የለም። “ ሲለው “አሃ ይህን ሁሉ መንገድ የመጣኅው በከተማ ያሉት ትልልቅ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ለሻንቆዎች እሺ ስለማይሉ ነው አይደል?” አለው። ምንም እኳን ሻንቆ ብሎ አጸያፊ የሆነውን ቃል ሲናገረው ቢናደድም ንዴቱን ዋጥ አድርጎ በመቻል፣ “አይ እንደማንኛውም ሰው ገንዘብ አለኝ የመጣሁት ገንዘብ ከፍዬ በአውሮፕላን ለመብረር ነው” ምን ዓንት ስሜት ለማወቅ ብቻ” አለው። አብሮት ያለው ወጣቱ ሰው “ኦ ፔርሲ ምን እንዲህ ያነጫንጭሀል ይህ ሰው ምንም ያደረገው ነገር የለም” ካለ ብኋላ ወደ ሮቢንሰን ዞር ብሎ “አትፍረድበት ይህ ሳምንት መጥፎ ነበር ለፔርሲ፣ ሞተሩ አልሰራ ስላለው ነው” ካለ ብኋላ እንደገና ወደ ጸጉረ ቀዩ አይሪሽ ዞሮ “ነገሩን ሁሉ ተወውና ተከተልኝ ለቢራ ወደከተማ እንመለስ” አለው። ከዚያም ጆን ዞር ብሎ እያየው “የአየር ሜዳው ዝግ ነው በከንቱ ነው የደከምከው ምንም ነገር እንዳትነካካ ወደመጣህበት የመመለሻ ጊዜህ ነው ” ብሎ መሄድ ሲጀምር “ሄይ አንድ ደቂቃ” ብሎ ጠራቸውና “የሞተሩ ብልሽት ምንድነው? ምናልባት እጠግነው ይሆናል፣ የምትሰጡኝ የበረራ አገልግሎት ይካካሳል” ብሎ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ሁለቱም ፊታቸውን ወደ ሮቢንሰን አዞሩና ፔርሲ “አንተ ልጅ አውሮፕላን አጠገብ ደርሰህ የማታውቅ መሆኑ እየታየ ስለ አይሮፕላን ምን ታውቃለህ?” ብሎ ጠየቀው። ይሄኔ ምጸቱ ተሰማውና “እኔ ልጅ አልባልም ስም አለኝ ጆን ሮቢንሰን እባላለሁ፣ እናም ስለበረራ ምንም ባላውቅ ስለሞተር ግን በመጠኑ አውቃለሁ፣ የሰለጠንኩ መካኒክ ነኝ” ሲለው “ይሁንልህ” በሚል ሁኔታ ባለማመንና የለበጣ መልስ ሰጥቶት መንገዱን ቀጠለ። ከግቢው ወጥተው አጥሩን ዞር እንዳለ ወጣቱ እየሳቀ “ፔርሲ አባቴ አይሪሾች ዱልዱም እራሶች፣ ባለጌዎች እና በጡንቻቸው እንጂ በጭንቅላታቸው የማያስቡ ናቸው ይል ነበር። አንተም እንደአባባሉ ሲበዛ ኩሩ ነህ። ቢራና የመሳሰለውን እንኳን ለራስህ መግዛት አትችልም። በአንዲት የማትሰራ ጄኒ(የአውሮፕላኗ ስም ነው) ተወጥረህ እና ታጥረህ ቁጭ ብለሃል። አሁን ደግሞ ይህ ሰውዬ የሚናገረው እውነት መሆኑና አለመሆኑን፣ እናም እውነት ከሆነ ወደስራህ ይመልስህ እንደሆነ ለማወቅ አትፈልግም?” ሲለው ፔርሲ ቀጥብሎ ቆሞ ወጣቱን አየት አደረገና ምንም ቃል ሳይናገር ወደ ግቢው ተመልሶ “እሺ ሮቢንሰን ምን ዓይነት የመካኒክነት ስራ እንደምትሰራ ንገረኝ” ሲለው “የተሽከርካሪ መኪናዎች ሞተር” ብሎ መለሰለት። “እንዴት ይህን ለማድረግ ቻልክ?” ሲለው የሶስት ዓመት የኮሌጅ ትምህርትና ዴትሮይት ውስጥ የሁለት ዓመት የስራ ልምድ እንዳለው እንዲሁም በአጥሩ ጥግ ያቆማትን የራሱን መኪና ሞተሩን አድሶ ገጣጥሞ የሰራው እሱ መሆኑን ነገረው። በመጨረሻም ፔርሲ ለጠየቃቸው ጥያቄዎች ሁሉ ሮቢንሰን አዎንታዊ መልስ ስለሰጠው ጥገናውን እንዲቀጥል ፈቀደለትና እሱና ወጣቱ ጓደኛው ወደ ቢራ መጠጫ ቤት ሄዱ።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ደራሲያን የፌስቡክ ገጽ

Leave a comment