ክፍል 2: ጥቁር አሜሪካዊው ፓይለት ኮ/ል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን የኢትዮጵያ ቡናማው ጆፌ (The Brown Condor of Ethiopia) ‘ብልጥ ልጅ የተሰጠውን ይዞ ያለቅሳል’

በዚህ የስራ ፈላጊ ጎርፍ ላይ ጥቁርነቱ ሲታከልበት ለጆን በሰለጠነበት የሞያ መስክ ስራ ማግኘት ዳገት የመግፋት ያክል አይሞከሬ ሆነበት። ምንም እንኳን በዚህ በሰሜኑ ክፍል የደቡቡን ያክል ባይሆንም ጥቁሮች መገለልና መገፋት እንዳለ ነበር የጠበቀው። መካኒክነት ለጥቁር የሚታሰብ ስራ አልነበረም። ጥቁር ስራ ከፈለገ ወይ ተላላኪ ወይ ጠራጊ መሆን ነው የነበረው ዕድል። ጆን ግን ተስፋ አልቆረጠም በመካኒክነት ሞያ ሰልጥኖ በላቀ ውጤት መመረቁን የሚመሰክርለትን ማስረጃውን ይዞ በየጋራዡ ደጅ መጥናቱን ተያያዘው። በስንት መከራ የረዳት መካኒክነት ስራ ቀንቶት ቢቀጠርም ዋናዎቹ መካኒኮች ነጮች ስለነበሩ ለጆን የሚሰጡት ስራ ጎማ ከመቀየርና ጥቃቅን የጥገና ስራዎችን ከመስራት የዘለለ አልነበረም። ‘ብልጥ ልጅ የተሰጠውን ይዞ ያለቅሳል’ እንዲል የሀገሬ ሰው ጆን ያለበትን ሁኔታ ሳያማርር በስራው አለቆቹን አሳምኖ ወደ ዋና መካኒክነት አደገ። ገቢው እየጨመረ ሲሄድም ከአሮጌ የመኪና መለዋወጫ ሱቆች እቃዎችን እየገዛ የራሱን መኪና ሰርቶ የመኪና ባለቤት ሆነ። ጆን ከስራ ውጪ ህይወትን በሙዚቃና በዳንስ የሚያጣጥም ወጣት ነበር። በዙ ተሰማ ስለ ጆን ታሪክ ባሰናዳው የሁለት አገር ጀግና በተሰኘ መጽሀፉ እንዲህ ይላል….. “ሮቢንሰን የስራ ሰው ብቻ አይደለም፣ መዝናናትም ያውቅበታል። ጊዜው የጃዝ ሙዚቃ፣ የኮንትሮባንድ መጠጥ ቤት ንግድ፣ ጥራዝ ነጠቅ የሆኑ ወጣት ሴቶች የፈሉበት ነበር። ስለሆነም በአንደኛው የከተማው ክፍል መዝናኛ ዳንስ ቤት እየሄደ በሚደንሰው ጥሩ ዓይነት አደናነስ ዝናን ስላተረፈ ቀበጥ ሴቶች ሁሉ የሱን ዝና ለመስማት ጊዜ አልፈጀባቸውም። በዛ ረዥም ቁመናው ላይ በደንብ ለብሶ በጨዋነትና በልበ ሙሉነት መንፈስ የሚደንሰውን ሰው አቅፋ ለመደነስ የማትመኝ ሴት አልነበረችም።” ከስራና ከመዝናኛው ባሻገር ጆን ቤቱ የሰበሰባቸውን በመካኒክነት፣ በንግድ አስተዳደርና በአየር ትራንስፖርት ዙሪያ የተጻፉ መጻፎችን በማንበብ ነበር ጊዜውን የሚያሳልፈው። በአይሮፕላን የመብረርና አይሮፕላን የማብረር የልጅነት ህልም የነበረው ጆን ህልሙ ቅዠት ሆኖ እንዲቀር አልፈቀደም። ገንዘብ አጠራቀመና በግል ገንዘብ እያስከፈሉ በትናንሽ አውሮፕላኖች ወደሚያሳፍሩ ድርጅቶች አቀና። ይህ ሀሳብ በዘመኑ ለአንድ ጥቁር ወጣት እንደ እብደትም ባይቆጠር አጉል ቅንጦት ሊባል የሚችል ነበር። ብዙዎቹ ድርጅቶች፣ ጥቁር ገንዘብ እንኳን ቢኖረው በአውሮፕላናቸው ለማሳፈር ይጠየፉ ነበር። ጆን ወደ አንድ የአውሮፕላን ድርጅት ሄዶ ያጋጠመውን ከላይ የተጠቀሰው ደራሲ እንዲህ ሰንዶታል…… “

ይቀጥላል

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ደራሲያን የፌስቡክ ገጽ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s